እምነታችን

Trinity

ምስጢረ ሥላሴ

«መቅድመ ኩሉ ንሰብክ ሥላሴ ዕሩየ ወቅዱስ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ከሁሉ አስቀድመን በአካል ልዩ በቅድስና (በክብር) አንድ የሆነውን ሦስትነት እንሰብካለን። ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው» ሲል ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) አስተምሮአል (ሃይማኖተ አበው፣ጎርጎርዮስ፣ ገጽ ፪፻፲)። የምስጢረ ሥላሴ መሠረቱና ምንጩ ቅዱስ መጽሐፍ ነው። የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት በሚገባ ጐልቶ የተገለጸው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባለመለወጥ ፍጹም ስው ከሆነ ወዲህ ነው። በመለኮት፣ በባህርይ (በህላዌ)፣ በፈቃድና በሥልጣን አንድ የሆነው እግዚአብሔር፣ የአካል፣ የገጽ፣ የስምና የግብር ሦስትነት እንዳለው የምናምነው እምነት ምስጢረ ሥላሴ ይባላል። በመለኮት አንድ የሆነው እግዚአብሔር፣ የአካል ሦስትነት አለው ማለት፣ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ይባላል ማለት ነው። በሌላም አነጋገር፣ ለአብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ ለወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ እንዳለው የምናምነው እምነት ምስጢረ ሥላሴ ይባላል። የሦስቱም (የሥላሴም) የስም ሦስትነት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ነው። የግብር ሦስትነታቸውም አብ ወላዲ ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ነው። ይኸውም፣ ወላዲነት፣ ተወላዲነት፣ ሠራፂነት ማለት ነው።

Incarnation

ምስጢረ ሥጋዌ

የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢር ማለት ነው። “ቃል ስጋ ሆነ... በእኛም አደረ” በሚለዉ የወንጌል ቃል ላይ የተመሰረተ ታላቅ የክርስትና ሃይማኖት ምስጢር ነዉ (የሐ 1፡14)። ይህ ምስጢር የእግዚአብሔር ልጅ፣ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለዱ (ሰው በመሆኑ) አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰው አምላክ የሆነበት ልዩ ምስጢር ነው። የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት ከመጣበት ሞት የዳነበት ምስጢር ነው። በተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን ‹‹ተዋሕዶ›› የሚለውን ስያሜ ያገኘችበት ምስጢር ነው። ሰማያዊው ለሰው ልጅ የተገለጠው በዚህ ምስጢር ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ ታላቅነት ሲናገር “የተነገረውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፣፤ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና” ብሏል። (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62፡4) ወልደ እግዚአብሔር፣ ወልደ ማርያም (የእግዚአብሔር አብ ልጅ የድንግል ማርያም ልጅ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት። የመጀመሪያው (ቀዳማዊ) ልደት ዘመን ከመቆጠሩ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ከሰው አእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢር (አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ) የተወለደው ልደት ነው (መዝ 2:7 መዝ 109:3 ምሳ 8፡25)። ሁለተኛው (ደኀራዊ) ልደቱ ደግሞ ዓለም ከተፈጠረ አዳም ከበደለ ከአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደው ልደት ነው (ገላ 4፡4 ኢሳ 7:14 ኢሳ 9:6 ዘፍ 3፡15 ፤18፡13 ፤ 12:8 ፣ መዝ 106፡20)። ዘመን የማይቆጠርለት፣ በቅድምና ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረ፣ ዓለምንም በአምላክነቱ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አካላዊ ቃል መለኮታዊ አካሉን፣ መለኮታዊ ባሕርይውን ሳይለቅ በተለየ አካሉ ንጽሕት፣ የባሕርያችን መመኪያ ከምትሆን ከድንግል ማርያም በሥጋ በተወለደ ጊዜ አምላካዊ አካልና ባሕርይን ከሰው አካልና ባሕርይ ጋር ያለመጠፋፋት፣ ያለመቀላቀል ተዋሐደ እንጂ አካሉም ባሕርይውም አልተለወጠም።

Baptism

ምስጢረ ጥምቀት

ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት ምስጢር ነው። ይህ ምሥጢረ ጥምቀት ከኃጢያት ነፃ የምንሆንበት ከዲያቢሎስ አገዛዝ አርነት የምንወጣበት ከእግዚአብሔር በጸጋ የምንወለድበት ምስጢር ነው። በቅዱሳት መጻህፍት እንደተገለጸው በነብየ እግዚአብሔር በቅዱስ ሕዝቅኤል ት.ሕዝ 36፡25 “ጥሩ ውሀንም ጥምቀትን እረጫችኋለሁ፡ እናንትም ትጠራላችሁ ከርኵሰታችሁ ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ አዲስ ልብ እሰጣችኋለው” በማለት የዚህን ምስጢር አስፈላጊነት አምልቶ አስፍቶ ተናገሯል። በዚህ ሀሳብ አበው ሐዋርያት ተባብረውታል። በምልአት ሰብከውታል። (የሐዋ.2፡38 ፣ 1ቆሮ 6፡11 ፣ ዮሐ. 3፡5 ፣ ኤፌ 5፡26 ፣ ገላ 3፡27 ፣ ቲቶ 3፡5)

Communion

ምስጢረ ቁርባን

ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት መባ ቁርባን ይባላል። ስለ ስርየተ ኃጢአት፣ ወይም ስለ ምስጋና፣ ወይም በስለት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ነገር ሁሉ ቁርባን ይባላል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢያት፣ በዕለተ ዓርብ ከመሰቀሉ በፊት በዋዜማው ሐሙስ ማታ፣ ከአስራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ ኅብስቱን አንስቶ ባርኮና ቀድሶ፣ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ፣ «ይህ ሥጋዬ ነው» ብሎ ሰጣቸው። ስለዚህ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር፣ወይኑንም በጽዋ አድርጎ ባርኮና ቀድሶ፣ «ይህ ደሜ ነው» ብሎ ሰጣቸው። ስለዚህ ወይኑ ተለውጦ ደመ ወልደ እግዚአብሔር መሆኑ ታላቅ ምስጢር ነውና ቁርባን ምስጢር መባሉ ስለዚህ ነው (ማቴ. 26፡26 ፤ ማር. 14:22 ፤ ሉቃስ 22:14-23)።

Resurrection

ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን

ትንሣኤ ማለት መነሣት፣ መቆም ማለት ነው። በተለይም ከሞትና ከመቃብር በሕይወት መነሣት ትንሣኤ ይባላል። ሞቶ ከተቀበረ አራት ቀን የሆነውን አልዓዛርን ጌታችን በቃሉ፣ «አልዓዛር ሆይ፤ ተነሣ!» ብሎ ከሞት አስነሣው፣ ከመቃብር አወጣው (ዮሐ. 11፡43-44)። ትንሣኤ ማለት ይህ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በተዋሐደው ሥጋ ከሞተና ከተቀበረ በኋላ፣ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ አማናዊ (እውነተኛው) ትንሣኤ ይባላል። ስዎች ከሞቱና ከተቀበሩ በኋላ፣ እንደገና ከፈጣሪያቸው ከእግዚአብሔር ሕይወትን አግኝተው ከሞትና ከመቃብር ይነሣሉ። ይህ ከሞትና ከመቃብር መነሣት፣ እጅግ ዐቢይና ድንቅ ነገር ስለሆነ፣የትንሣኤ ምስጢር ተብሎ ይጠራል።